Main menu

Summary report on Home Grown Economic Reform Agenda

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን (ኢኢአ) “የዕድገትና ለውጥ ራዕይ ለኢትዮጵያ፤ ትላልቅ ሀገራዊ ግቦችና ፈታኝ ሁኔታዎች” በሚል ዓብይ ርዕስ ሥር ከሚያካሂዳቸው ተከታታይ ውይይት ውስጥ

መድረክ 4፡ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፤ ወደ ብልጽግና ጉዞ በሚል ሀሳብ ላይ የተደረገ   ውይይት አጭር ዘገባ

I.      መግቢያ

በየኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፤ ወደ ብልጽግና ጉዞ በሚል ሀሳብ ላይ” በሚል ርዕስ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል የግማሽ ቀን ፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ውይይት የብሔራዊ ባንክ ተወካይን ጭምሮ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በንቃት ተሳትፈዋል፡፡ ለታዳሚዎቹና ተጋባዥ እንግዶች የውይይት የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ተመራማሪዎች በሀገራችን በርካታ ምርምሮች ያካሄዱና ረጅም ልምድ ያካበቱ አቶመሠለ ምናለዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ እና ዶ/ር ኢዮብ ተስፋዬ ሲሆኑ መድረኩን በመምራት በኩል ደግሞ ዶ/ር አለማየሁ ሥዩም ተሳትፈዋል፡፡ በመቀጠል በማሻሻያው አስፈላጊነት፣ ዝግጅት፣ ይዘት እና አተገባበር ላይ መወያያ ሀሳቦች ተስተናግደዋል፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ሥር በሰደደ የመዋቅራዊ መዛባት ችግሮች ውስጥ ይገኛል፡፡ የሥራ አጥነት፣ የግብርና ምርታማነት አለማደግ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ የውጭ ዕዳ ጫና እና ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ እድገት በዋነኛነት የሚጠቀሱ የኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡ ከዚህ ሥር የሠደደ የኢኮኖሚ ችግር ለመውጣት የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ፕሮግራም እና የረዥም ጊዜ የልማት እቅድን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መግባት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በዚህ መሠረት መንግስተ መሪነቱን በመውሰድ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ረቂቅ ሠነድ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል፡፡ የዚህ ውይይት አላማ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ጥልቅ ዳሠሳ በማድረግ ጠቃሚ ግብዓተቶችን መስጠት ነው፡፡

II.      የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ

አቶ መሠለ ምናለ መንግስትን በመወከል አጀንዳው ሀገር በቀል የመሰኘቱ ምክንያት አሁን ሀገራችን ለገጠማት ለየት ያለ ኢኮኖሚያዊ ችግር ለየት ያለ መፍትሄ ለማቅረብ ጥረት የሚያደርግ የሪፎርም አጀንዳ በመሆኑ እንደሆነ እና መንግስት ያለማንም ግፊት በራሱ ኢኮኖሚው ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው አምኖበት ያዘጋጀው በመሆኑ እንደሆነ ማብራሪያ በመስጠት ረቂቁ ያለቀለት፣ የበሰለ እና ምንም የማይጨመርበት ወይም የማይቀነስበት ሠነድ ሳይሆን ግብዓት ለማሰባሰብ የቀረበ እንደመሆኑ ተሳታፊዎች በነፃነት ግብዓት እንዲሰጡበት ጥሪ ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም የኢኮኖሚ ማሻሻያው መነሻ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ፣ ከሪፎርሙ የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች ኣና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልግ አቅምና ሀብት የሚሉ ሃሳቦችን አቅረበዋል፡፡

1)    የኢኮኖሚ ማሻሻያው መነሻ

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለፉ ስኬቶችን መነሻ አድርጎ እና ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የተጀመረውን የኢኮኖሚ ለውጥ ለማስቀጠል የተዘጋጀ ነው፡፡  ለነባር ተግዳሮቶችን መፍትሄ መስጠት እና ሌሎች አዳዲስ እድሎችን መፍጠር እንዲሁም ከዘመኑ ጋር የሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን እና ፋላጎቶችን ማስተናገድም ሌሎቹ ዓላማዎች ናቸው፡፡ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ ፖሊሲዎች እና ተቋማት የኢኮኖሚውን ግዝፈት በሚመጥን መልኩ አብረው አቅማቸው እንዲያድግ  ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ነጥቦች ማሻሻያውን ይበልጥ አስፈላጊ ያደርጉታል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አመታት ባለሁለት አሀዝ ማደጉን ፣ የነፍሰወከፍ ገቢ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን፣ የድህነት ምጣኔ መቀነሱን፣ ምርታማነት መጎልበቱን፣ በጤና እና ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን እንዲሁም በመሠረተ ልማት ግንባታ ትልቅ እመርታ መታየቱ በኢኮኖሚ ማሻሻያው የቀደሙ ስኬቶች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል፡፡ የስኬቶቹ ምንጭ የመንግስት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ መሆኑ ታይቷል፡፡ ከፋይናንስ ምንጮቹ መካከል ቁጠባ (Domestic Saving) ተጠቅሷል፡፡ የቁጠባ መጠን ከ10 በመቶ ወደ 24 በመቶ ገደማ መድረሱ በመንግስት ከተተገበሩ የቤቶች ቁጠባ፣ የጡረታ አበል ቁጠባ እና የመሳሰሉ ምክንያቶች ጋር ተያይዟል፡፡ ሆኖም የቁጠባው መጠን እድገት ያሳይ እንጂ በቂ ስላልነበር የውጪ ብድር እና ድጋፍ አስፈለጓል፡፡

ከስኬቶቹ በመለስ በርካታ የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ጎራ ለመቀላቀልና ዝቅተኛውን መሥፈርት ለማሟላት የነፍስወከፍ ገቢ በሶስት እጥፍ ማሳደግ፣ የድህነት ምጣኔ በግማሽ መቀነስ እና መሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቀናል፡፡ ለምሳሌ በውሃና ኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ40-45 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅብናል ፡፡ በዚህ ረድፍ ለመገኘት የያዝነው እቅድ  በሶስት እጥፍ ማደግ አለበት፡፡

መዋቅራዊ ሽግግር መፍጠር አለመቻል ሌላው ድክመት መሆኑ ታይቷል፡፡ የቀደመው እድገት ኢንቨስትመንትን እንጂ ምርትና ምርታማነትን መሠረት ያደረገ አለመሆኑ ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ ግብርና የቀጣሪነት ድርሻ እና የማኑፋክቸር ዘርፉ የውጪ ንግድ ድርሻ እንደማሳያ ቀርቧል፡፡ ግብርና በGDP ያለው ድርሻ ከ60 በመቶ ወደ 30 በመቶ ወርዷል፡፡ በቀጣሪነት ግን ከ70 በመቶ አካባቢ ብዙ አልተለወጠም፡፡ ማኑፋክቸር ዘርፉ የውጪ ንግድ አሁንም 10 በመቶ ገደማ ነው፡፡ መካከለኛው ገቢ ሀገሮች ይሄንን በአማካይ 60 በመቶ ገደማ አድርሰውታል፡፡

ከዚህ ሌላ የተለዩ እና ከሴክተሮች ጋር የሚያያዙት ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በግብርና የግብዓት አቅርቦት፣ የመሬት ይዞታና ዋስትና፣ መሠረታዊ መሠረተ ልማት ውስንነት፣ የገበያ ስርጭት እንዲሁም ለዘርፉ የተለዩ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡ በዘርፎቹ የእርስበርስ ግንኙነትና ተመጋጋቢነት /Backward and forward linkage/ ላይም እንደዚሁ ክፍተቶች ተለይተዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከውጪ በሚሸመቱ ግብዓቶች ላይ የበዛ ጥገኝነት ተስተውሏል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂም የተለያዩ ሴክቶራል ችግሮች ተለይተዋል፡፡

የውጪ ምንዛሬ አቅማችንን ያሳድጋሉ ተብለው የተጀመሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በጊዜ አለመጠናቀቅ ሌላ ተግዳሮት ነው፡፡ የተከማቸ የውጭ ዕዳም ከውጪ ንግድ ገቢ መዳከም ጋር ተጨምሮ ጫና ውስጥ አስገብቶናል፡፡ ለግሉ ዘርፍ የሚቀርበው የፋይናንስ መጠን እጅግ ያነሰ ከመሆኑ በቂ የሥራ እድል በመፍጠሩ በኩል አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በገበያው ላይ የዋጋ ንረት ታይቷል፡፡

2)   የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ

የኢኮኖሚ ማሻሻያ በፖሊሲ ማዕቀፉ ሶስት ምሰሶዎች አሉት፡፡ እነዚህ ምሰሶዎች የማክሮኢኮኖሚ፣ የመዋቅራዊ ወይም ተቋማዊ እና ሴክተር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በሶስቱ ክፍሎች የተመለከቱትን ማነቆዎች ኢላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ ዋነኞቹ ግቦችም የስራ እድል መፍጠር፣ ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ፣ ድህነትን መቀነስ እና ኢኮኖሚውን በማበርታት ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር ነው፡፡

ማክሮኢኮኖሚ ሚዛን ካልተስተካከለ ኢንቬስተሩ፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና ሸማቹ በኢኮኖሚው ላ እምነት እነዳይኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንን ለመለወጥ ማሻሻያው /ሪፎርም/ የውጪ ምንዛሬ፣ ፋይናንሺያል ሴክተር፣ ፐብሊክ ሴክተር እንዲሁም ሞኒተሪ እና ፊስካል ሴክተሮችን ይነካል፡፡ እነዚህ ማሻሻያዎች እርስበርሳቸው ተደጋጋፊ እና የኢኮኖሚውን እድገት ዘላቂነት ባለው መልኩ የሚደግፉ ሲሆኑ የዕዳ ጫናውን በመቀነስ በኩል ሚናቸው ትልቅ ይሆናል፡፡

ለዚህ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ፊስካል ፖሊሲ መከተል ወሳኝ ነው፡፡ የውጪ ምንዛሬ ገበያውን በተመለከተ የአጭር እና ረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል፡፡ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር /Privatization/፣ የዕዳ ጫናን የማያስከትሉ የውጪ ብድር /Concessional Loan/ እና ከውጪ ሀገር በሀዋላ ለሚላኩ ምንዛሬዎችን /Remittance/ የማበረታቻ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ከአጭር ጊዜ መፍትሄዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የውጪ ምንዛሬ አቅማችን በዚህ መልኩ ሲሻሻል በሂደት ወደ ምንዛሬ ገበያ አሠራር ማሻሻያ /Market Reform/ እንሄዳለን፡፡ የፋይናንስ አቅርቦትን /Access to finance/ ለማሻሻል የፋይናንሺያል ሴክተር እና የካፒታል ገበያ /Capital Market/ መፈጠርና መጎልበት በከፍተኛ ሁኔታ ይረዳል፡፡

ሴክተርን በተመለከተ በተለየ መልኩ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ተለይተዋል፡፡ በተለይ በግብርና የግብዓት አቅርቦትን እና ውጤታማነቱን ከማሻሻል ጀምሮ እንደ መስኖ ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ማስተካከል፣ የመሬት አጠቃቀም እንዲሁም የግብርና ልዩ ፋይናንስ እና ኢንሹራንስ ማዘጋጀት ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ሌሎችም ዘርፎች ማነቆዎች ተለይተው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

3)   ከሪፎርሙ የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ዕቅድ የኢኮኖሚ እድገቱን እያስቀጠለ በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ /በቀጣዮቹ ሶስት እና አራት አመታት/ የማክሮኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ማስተካከል ነው፡፡ በማሻሻያው የሚጀመሩ ስራዎች በቀጣይ እየተዘጋጀ ካለው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ጋር የሚጓዙ ናቸው፡፡

4)    የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልግ አቅምና ሀብት

ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገው ሀብት የሚገኘው ሀገራዊ ቁጠባን በመጨመር፣ የመንግስት ተቋማትን ድርሻ ወደ ግል በማዞር እና የዕዳ ጫና የማይፈጥሩ የውጪ ብድሮችና የፋይናንስ ድጋፎች በማሰባሰብ ይሆናል፡፡

III.      በረቂቅ አጀንዳው ውይይት ላይ የተነሱ ሀሳቦችና ግብዓቶች

ከዚህ በታች የተጠቀሱ ሀሳቦች በተቺዎችና በተሳታፊዎች እንደገብአት ቀርበዋል፡፡

 • የማክሮኢኮኖሚው ችግሮች ሳይፈቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሊስተካከል አይችልም፡፡ የሀገራችን ኢኮኖሚ ችግር ደግሞ በምርታማነት ፣ ስራ ፈጠራ፣ የውጪ ምንዛሬ ማምጣት ላይ ያለ ድክመት እንደመሆኑ ማሻሻያው መዋቅራዊ ማስተካከያዎችን ማንሳቱ እንደ ትልቅ እርምጃ ተጠቅሷል፡፡
 • ማሻሻያው ያለፉ ስኬቶችን እውቅና ሰጥቶ እና የተሰሩ ስራዎችን እንደመነሻ ወስዶ መነሳቱ በኢትዮጵያ አስተዳደራዊ /ሥርዓት/ ለውጦች ጊዜ ከተለመደው ያለፈውን ጨርሶ በዜሮ አባዝቶ ወይም አፍርስ እንደ አዲስ ከመጀመር አባዜ የወጣ መሆኑ እንደበጎ ነገር ተወስዷል፡፡
 • ፊስካል ፖሊሲን ታሳቢ አድርጎ ከመንግስት ወጪ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም  የውጪ ብድር ጫናው ታሳቢ መደረጋቸው ሌላው ትልቅ አዎነታዊ መነሻ መነሻ ተደረጎ ተወስዶእል፡፡
 • የቀደመውን ስኬት እውቅና መስጠት ተገቢ ቢሆንም ጠቀሜታቸውን የጨረሱ ፖሊሲዎችን ተመልክቶ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሶአል፡፡
 • በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተመዘገቡት ስኬቶች እንዳሉ ሆነው በግልጽ የታዩ ድክመቶችን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ የዕቅድ ማስፈጸሚያ ፋይናንስ ምንጭን ጥርት ባለ ሁኔታ አለማስቀመጥ እና ደካማ ተቋማዊ ብቃት ያስከፈለው ዋጋ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡
 • የማክሮኢኮኖሚውን ሁኔታ "የማክሮኢኮኖሚ የሚዛን መዛባት" ብቻ ብሎ መግለጽ ችግሩን ያሳንሰዋል፡፡ "የማክሮኢኮኖሚ ቀውስ" ውስጥ ነን፡፡ ከፍተኛ የኑሮ ንረት፣ የከፋ መዋቅራዊ ቀውስ፣ አስከፊ የውጪ ምንዛሬ ችግር፣ የከበደ የውጪ ዕዳ ጫና እና የተጋነነ የውጪ ንግድ ሚዛን መዛባት አለ፡፡
 • ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ድክመት የMonetary Policy ነው፡፡ ከምርትና ምርታማነት ጋር ያልተያያዘ የገንዘብ ህትመት ለተፈጠረው የዋጋ ንረትና የንሮ ውድነት ዋንኛው መንስኤ ነው፡፡
 • በማሻሻያው አጀንዳ የንግድ ፖሊሲው በተገቢው መልኩ ቦታ አላገኘም፡፡ የውጪ ንግድን ማሳደግ እና ተፎካካሪ የምርት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማዘጋጀት ከተፈለገ የንግድ ፖሊሲው ራሱን ችሎ በዝርዝር መታየት እና መፍትሄ ሃሳቦች ሊቀርቡበት ይገባል፡፡
 • የውጪ ምንዛሬን በገበያ ዋጋ ለመወሰን መፍጠን የለብንም፡፡  አስቀድመን የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ስራዎች ካልሰራን የውጪ ምንዛሬውን ለገበያ መተው አደገኛ ይሆናል፡፡
 • የካፒታል ገበያ መጀመር የፋይናንስ አቅርቦትን ሊያግዝ ቢችልም ሌሎች ሀገሮች (የተሻለ ጠንካራ ኢኮኖሚ የነበራቸው) ሲጀምሩት የገጠማቸውን ችግር እና ቀውስ በጥልቀት ቢታይ ጥሩ ነው፡፡  
 • የግል ክፍለ ኢኮኖሚያችን አሁንም ሀላፊነትን ለመሸከም የችሎታና አቅማቸው ነገር ከግምት ሊገባ ይገባል፡፡
 • ማሻሻያውን ለማቀድና ለመተግበር መሠረት የሚሆነን ሀገራዊ ስታቲስቲክስ ተዓማኒነትም በተለየ ጥንቃቄ ቢታይ
 • በሀገራችን ከተሜነት (በከተማ የሚኖረው ህዝባችን ቁጥር) በዕጥፍ እየጨመረ እና የራሱን ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ይዞ እየመጣብን ነው፡፡ በማሻሻያው አጀንዳ ይሄ ትኩረት አግኝቶ ቢካተት መልካም ይሆናል፡፡       

የሚሉ ናቸው፡፡