Main menu

Summary report on Agricultural Transformation

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚከስ አሶሴሽን ‘‘የዕድገት ለውጥ ራዕይ ለኢትዮጵያ፡ ትላልቅ ሀገራዊ ግቦችና ፈታኝ ሁኔታዎች ’’ በሚል ርዕስ ስር ከሚያካሂዳቸው ተከታታይ የውይይት መድረኮች ውስጥ

መድረክ  3  የአገራችን ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግዳሮቶች ፡ ተፈጥሮ  የለገሰንን ተነጻጻሪ ጥቅም (competitive advantage)  ለመጠቀም ያለመቻላችን ሚስጥሩ ምን ይሆን? በሚል ርዕስ ዙሪያ የተደረገ ውይይት አጭር ዘገባ

1.   መግቢያ

በየኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን “የሀገራችን ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግዳሮቶች፣ ተፈጥሮ የለገሰንን ተነፃፃሪ ጥቅም (Competitive Advantage) መጠቀም አለመቻላችን ሚስጥሩ ምን ይሆን?” በሚል ርዕስ ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ውይይት ክቡር ዶ/ር ኢያሱ አብርሃ፣ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የግብርና ሚኒስትር  ከፍተኛ አማካሪ ጨምሮ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በንቃት ተሳትፈዋል፡፡ ለታዳሚዎቹና ተጋባዥ እንግዶች የውይይት የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ተመራማሪዎች በሀገራችን ግብርና ዘርፍ በርካታ ምርምሮች ያካሄዱና ረጅም ልምድ ያካበቱ ዶ/ር ኢያሱ አብርሃ፣ ዶ/ር ጌታቸው ድሪባ እና ዶ/ር ገዛኸኝ አየለ ሲሆኑ መድረኩን በመምራት በኩል ደግሞ ዶ/ር ብርሃኑ ደኑ ተሳትፈዋል፡፡ የውይይቱ ዓላማ በዋናነት ግብርናውን በማሻሻል የሀገራችን የምግብ ዋስትናን ከማረጋጋጥ በተጨማሪ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ መንግስትና  ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ለመወያየት ነው፡፡

2.   በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ መዋቅራዊ ችግሮች

በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑ (Rain-fed agriculture) እና አርሶ አደሩ በተበጣጠሰና በአነስተኛ እርሻ መሬት ላይ መመስረቱ ዋንኛ መዋቅራዊ ችግር ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ አርሶ አደር አባወራ የመሬት ይዞታ ሲታይ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆነው አርሶ አደር 1 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ፣  ከ1ሺህ እስከ 5 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ያላቸው አርሶአደር አባወራዎች 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን (35 በመቶ አርሶ አደሮችን የሚያካትት) ሲሆኑ እስከ 1 ሄክታር መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች 4 ሚሊዮን ናቸው፡፡ በጥቅሉ ከ1 ሄክታር በታች መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች 67 በመቶ ናቸው፡፡ይህ የሚያሳየው የመሬት ይዞታው ጠባብ በመሆኑ በዚህ ላይ ምን መስራት ይቻላል የሚለው ጉዳይ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡

ከዚህ ጋር የሚያያዘው የመሬት ጉዳይ ህገ-መንግስታዊ ችግር ያለበት መሆኑ ነው፡፡ መሬቱ የግሌ ነው የሚል አርሶ አደር እስካልተፈጠረ ድረስ እና መሬቱን ምርታማ ለማድረግ ወጪ እስካላወጣ እንደዚሁም እንደማንኛወም ንብረት ለማሲያዣነት እና ለመለወጥ እስካልቻለ ድረስ ግብርናውን ትራንስፎርም ማድረግ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በመሬት ይዞታ እና በኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ ምክንያት የግብርናው ዘርፍ ምርታማ አይደልም፡፡ ይሀን ለማሳየት አንድ የደቡብ አፍሪካ አርሶ አደር ከኛ አርሶ አደር ጋር ሲነፃፀር 21 ጊዜ ምርታማ ነው፣ የግብፅ አርሶ አደር 11 ጊዜ ምርታማ ሲሆን ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ሲነፃፃር ደግሞ የአንድ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርታማነቱ በ2.6 ጊዜ ያንሳል፡፡ ይህ የሚያሳየው የግብርናው ዘርፍ እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የግብርና ምርቶቻችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አይደሉም፡፡ ለአብነትም የስንዴ ዋጋ ከዓለም ገበያ 3 እጥፍ የሚጨምር ሲሆን የሰሊጥ ዋጋ ደግሞ የሚሸጠው ከአገር ውስጥ ባነሰ  ዋጋ ነው፡፡

ግብርናው ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እድገት (Gross Domestic Product) GDP ያለው አስተዋጽኦ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ብሎአል በሚል የግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቶአል እየተባለ የሚሰጠው የተሳሳተ መረጃ በራሱ ችግር ሆኖ ሳለ ለዘረፉ ሊሰጥ ስለሚገባው ትኩረት የተዛባ እንዲሆን ያስችላል የሚል ስጋት አሳድሮአል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩ ቁጥር መጨመር (17 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደር)፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ስርጭትን  በበቂ ሁኔታ ማዳረስ አላስቻለም፡፡  በመሆኑም  ባለፉት ዓመታት አማካይ የምርት እድገት ከ13 ኩንታል ወደ 26 ኩንታል እድገት ቢያሳይም ይህ እድገት መዋቅራዊ ለውጥ እንዳላመጣ ተገልጾአል፡፡  በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢ መሬት እየተራቆተና ተፈጠሮ ሃብት እየተማናመነ መምጣቱ የገፀ- ምድርና የከርሰ-ምድር የውሃ ሀብታችን በእጅጉ እየጎዳው እንደሆነ ተጠቁሞአል፡፡

ሌላው በመንግስት በኩል ለሐገር ውስጥ ባለሃበት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን  ሊታረም የሚገባው ችግር እንደሆነ ተጠቅሶአል፡፡ በተለይም መንግስት ለውጭ ኢንስትመንት በፖሊሲ የተደገፈ ማትጊያ የሰጠ ቢሆንም ለሐገር በቀል ኢንቨስትመንትና ኢንቨሰተሮች ግን የሚሰጠው ማትጊያ አናሳ መሆኑ የግብርናው ዘርፍ ወደ ኮሜርሻላይዜሽን የሚያደረገውን ጉዞ በእንጭጩ ቀጭቶታል፡፡ ለውጭ ኢንቨሰትመንት የተደረገው እስከ 85 በመቶ የሚደርስ ብድር፣ እንዲሁም ከ4-5 ዓመታት የታክስ እፎይታ ተጨባጭ ለውጥ ካለማምጣቱ በተጨማሪ መንግስት ያዘጋጀው 3.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቷል፡፡ ይህም መንግስት በዚህ ዘርፍ በውጪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያደረገው ክትትልና ቁጥጥር ደካማ መሆኑን ያሳያል፡፡ በእንስሳት ልማት ዘርፍ ያለውም ኢንስትመንስት ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ ብዙዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት በግብዓት አቅርቦትና በተለያዩ ምክንያቶች እንዳቋረጡ ተገልጾአል፡፡ ባንኮች ለዘርፉ ብድር ለመስጠት የሚቸግሩ መሆኑ ሌላው መዋቅራዊ ችግር መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡

ዘርፉ ላይ መንግስት እያደረገው ያለው ከፍተኛ ወጪ ጥረትም ዘርፉን ትራንስፎርም ለማድረግ እንዳላስቻል ተጠቁሞእለ፡፡ በዚህ በኩል  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ከገባችው በየዓመቱ የ10 በመቶ ዓመታዊ በጀት ምደባ ከፍ ባለ ደረጃ 14 በመቶ ስትመደብ ብትቆይም ሀገሪቱ ያላትን “comparative advantage”  ወደ “competitive advantage” መለወጥ አልቻለችም፡፡ ከ67 ሺህ ያላነሰ የግብርና የልማት ሠራተኞች ቢኖሩም ይህን እድል ወደ ምርትና ምርታማት መለወጥ አልተቻለም፡፡

3.   የቀረቡ የመፍትሄ ሃሳቦች

በአሁኑ ወቅት ግብርና ዋና የሀገራችን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ያስገነዘቡት ተመራማሪዎቹ  ከጠቅላላው ህብረተሰብ 80 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሬ እና ለአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የግብዓት ምንጭ ከመሆን ባሻገር የኢንቨስትመንት ካፒታልና ገበያ በመፍጠር ረግድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ትልቅ እምቅ ሐብት (Huge potential) በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማትን ለማሳደግ በሳይንሳዊ መንገድ መመራት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በእውቀት የዳበረ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች የግብርና ስራዎችን መከወንና መምራት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት አቅራቢዎቹ ይህም ዘርፉን ወደ መካናይዜሽንና ኮመርሻላይዜሽን ለማሸጋገር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ተስማሚ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ግብርናውን በቀጥታ ሊደገፍ የሚችል የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት፣ የአመራሩን፣ የባለሙያውንና አርሶ አደሩን ቁርጠኝነት ማሳደግ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት እና ምርምር ተቋማት ጋር ትስስርና ቅንጅት መፍጠር ብሎም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ግብርናን ለማዘመን የማይተካ ሚና እንደላቸው ተገልጾአል፡፡

በግብርናው ዘርፍ እውቀት ያላቸው ባለሀብቶች እንዲሳተፉና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታታትና መደገፍ እንዳለባቸው ተገልጾአል፡፡  ዘመናዊ የአስተራረስ ዘይቤ በስፋት ለመተግበር እንዲቻልም መንግስት ከምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት አለበት፤ ከዝናብ ተኮር እርሻ ወደ መስኖ ተኮር እርሻ በመሸጋገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መጣር ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

67 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ከአንድ ሄክታር ያነሰ በመሆኑ ጉልበት፣ ቴክኖሎጂ እና ግብዓቶችን በምን መንገድ ብንጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል የሚለው ጥያቄ አፋጣኝ መልስ የሚጠይቅ መሆኑ ተስምሮበታል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በአግባቡ መስራት የተመናመኑ ብዝሃ ሕይወት እንዲያገግሙ ከማድረግ በሻገር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወደር የለሽ መፍትሄ እንደሆን ተጠቅሶአል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራችን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማረጋገጥ እንድትችል ከህገ-መንግስቱ ጀምሮ የግብርና ፖሊሲ ጉድለቶችን ፈትሾ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑ ተገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በህገ መንግስቱ በመሬት ባለቤትነት ዙሪያ የተቀመጠው ድንጋጌ በማሻሻል ቢያንስ መሬት በሊዝ ስርዓት መሸጥ፣ መለወጥና ማስያዝ እንዲቻል በማድረግ የባለቤትነት ስሜት ማሳደግ ካልተቻለ ግብርናውን ለማዘመን አዳጋች እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

መንግስት ለውጭ ኢንስትመንት የሚሰጠውን ማትጊያ ለሐገር በቀል ኢንቨስትመንትም በአግባቡ መስጠትና መደገፍ እንደሚገባ የሚሰጠውም ድጋፍ የታሰበለትን ዒላማ እንዲመታ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ተጠቅሶአል፡፡ የሀገራችንን ግብርና ለውጥ እውን እንዲሆን ለማስቻል በማርኬቲንግ ስትራቴጂ ላይም በተለይ በ “Branding, Certification, Standardization” በመሳሰሉት ጉዳዮች የተሻለ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅ ተመልክቷል፡፡ የቡና ቱሪዝም ማቋቋም፣ “Coffee Specialty” እንዲኖር መስራት፣ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ እና የመሳሰሉት ተቋማትን ራሳቸውን እንዲፈትሹና ውስጣዊ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ ጥረት ማደረግ የግብርና ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተመክቷል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ሦስት አስተሳሰቦች መፈተሸ እንዳለባቸውም ተነስቷል፡፡ የመጀመሪያው አርሶ አደሩ ላይ ምሁሩ ያለው አመለካካት ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ብዙ ጊዜ እንደ ነፃ አውጪ፣ የማይቀየር፣ የለውጥ ኃይል ሊሆን የማይችል ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ ሁለተኛው በምግብ ራስን መቻል ማለት ሁሉንም ነገር ማምረት እንደሆነ ይነገራል ይህ መሆን የለበትም የምግብ ዋስትና ሲባል ከፊሉን በማምረት፣ ከፊሉ ደግሞ በገበያ እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል  መታሰብ አለበት፡፡ ሶስተኛው  ስለነጋዴ ያለን አስተሳሰብ ነው፡፡ ነጋዴውን ቢዙ ጊዜ የምንስለው አጭበርባሪ እና አምራች ያልሆነ በሚል ነው፤ ይህ አመለካከት መስተካከል እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በመጨረሻ በሀገራችን ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ተመሳሳይ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን የመወያያ ርዕስ፣ ጊዜና መሰብሰቢያ ቦታ በአሶሴሽኑ በኩል በቅርብ እንደሚገለፅ በማስታወስ ሦስተኛው መደበኛ የውይይት መድረክ በዚህ ተጠናቋል፡፡