Main menu

Summary Report on the State of Financial Inter mediation and the Resilience of the Ethiopian Financial System

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስ አሶሴሽን ‘‘የዕድገት ለውጥ ራዕይ ለኢትዮጵያ፡ ትላልቅ ሀገራዊ ግቦችና ፈታኝ ሁኔታዎች ’’ በሚል ርዕስ ስር ከሚያካሂዳቸው ተከታታይ የውይይት መድረኮች ውስጥ

 

ረክ 2፡ የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት ወቅታዊ ቁመናና ለውጥን የመቋቋም ብቃት ላይ የተደረገ ውይይት አጭር ዘገባ

1.   መግቢያ

በአሶሴሽኑ አዘጋጅነት “የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ወቅታዊ ቁመናና ለውጥን የመቋቋም ብቃት” በሚል ርዕስ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል የፓናል ውይይት ተካሂዶአል፡፡ በውይይቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተወካይን ጨምሮ የዘርፉ ምሁራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበታል፡፡

በተጠቀሰው  ርዕስ ዙሪያ  በዘርፉ እውቅና ያላቸው ዶ/ር ገብረ ህይወት አገባ፣ አቶ ሚካኤል አዲሱ እና ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን በሀገራችን የፋይናንስ ዘርፉ ቁመናና ችግርን የመቋቋም ብቃት ላይ መሠረት ያደረጉ የፋይናንስ ተደራሽነት፣ ቁጠባን ማስፋፋት፣ የብድር አቅርቦትና አስተዳደር እንደዚሁም የብሔራዊ ባንክ ሚና ላይ ያተኮሩ የውይይት መነሻ ሃሳብና ማብራሪ ያቀረቡ ሲሆን ዶ/ር እዮብ ተስፋዬ ውይይቱን መርተውታል፡፡

በአቅራቢዎቹ የተመለከቱት ሃሳቦች በዋናነት የፋይናንስ ዘርፉን በማሻሻል እና ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ በሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትና ግንባታ ዙሪያ ሁለንተናዊ ሚና መጫዎት እንዲችሉ፤ ዘርፉ ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ፍትሃዊ የፋይናንስ ተቋማት ስርጭትን የሚያረጋግጥ ስርዓት ለመዘርጋት መደረግ ያለባቸውን የማሻሻያ ሃሰቦች ጭምር የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ በሀገሪቱ ያለውን የህዝብ ቁጥር መጨመርና የወጣቱን ስራ ስምሪት ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት፤ ለዚህም የተሻለ ልምድ ካላት የቻይና የእድገት “job opportunity oriented growth” ስትራቴጂ ልምድ በመውሰድ  የፋይናስ ዘርፉን ሥራ ፈጣሪነት ማጎልበት እንዳለበት ተጠቁሞአል፡፡

 

2.  የፋይናንስ ተደራሽነት

የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ፍትሃዊ፣ አሳታፊ እና ሁሉን አቀፍ እድገትና ልማት ለማረጋገጥ የገጠሩን ህዝብ፣ ሙስሊሙን ማህበረሰብ፣ ሴቶችን እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ መሆን እንዳለበት ተገልጾአል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ የሁሉን ማህበረሰብ ፍላጎት ያማከለ እንዲሆንና ለሀገር ልማት ተደራሽ ለማድረግ ባንኮች የቅርንጫፍ አድማሳቸውን ማስፋፋት፣ በቅርንጫፍ መድረስ የማይቻልበትን ደግሞ በቴክኖሎጅ (ለአብነት ሞባይል ባንኪንግ) በመጠቀም እንዲስፋፉ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑ ተመልክቷል:: በሌላ በኩል አንዳንድ ሃገራት “Plowback Policy” ማለትም በቁጠባ መልክ ከተሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን መቶኛ እዛው አካባቢ በብድር መልክ መስጠት እንደ ፖሊሰ አማራጭ በመውሰዳቸው አካታች (inclusiveness) የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ችለዋል፡፡ በመሆኑም ይህን ተሞክሮ በአገራችን ሊሞከር እንደሚገባ ሃሳብ ቀርቦአል፡፡

የሀገሪቱን ኢንቨስትመንት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የተቋማቱን አሰራር ዘመናዊ ማድረግ እና ተወዳዳሪነታውን ማሳደግ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑ ላይ ሃሳብ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፍ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በዋናነት በአዲስ አበባና ሌሎች ክልል ከተሞች ላይ የተከማቹ በመሆኑ (ለአብነት በአዲስ አበባ ከ30 እስከ 35 በመቶ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በክልል ከተሞች) በመሆኑ በገጠር የሚኖረውን ከፍተኛ የሀገሪቱን የህዝብ ቁጥር ያላገናዘበ ስለመሆኑ ተገልጾአል፡፡ በዚህ ረገድ 75 በመቶ ያህል ሕዝብ የፋይናስ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለ ይህንንም በቴክኖሎጂ ለመድረስ እንዳይቻል ባንኮች ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ማበረታቻ እና የውድድር ሜዳ ስለሌለ ቴክኖሎጂ ተኮር የፋይናስ አገልግሎት ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ በተጨማሪም ከህዝቡ ፍላጎት አንፃር የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡት የምርትና አጠቃላይ የአገልግሎት ፓኬጆች ከተጠቃሚዎችና ደንበኞች ፍላጎት ጋር አለመመጣጠን የሚስተዋልበት መሆኑን የጠቆሙት ተናጋሪዎች ብድር ለማግኘት ማስያዣ (ኮላተራል) የግድ ነው፤ ይህም አብዛኛው የሀገራችን ወጣቶችን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘ በመሆኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ያላደረገ አካሄድ መሆኑ ተገልጾአል፡፡

 

3.  ቁጠባን ማስፋፋት፣ የብድር አቅርቦትና አስተዳደር

በፋይናንስ ዘርፉ የተካሄደው ቁጠባን የማሳደግ እንቅስቃሴ (Deposit mobilization) ውጤታማ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቁጠባ ከጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት አንጻር 24 በመቶ ደርሶአል፡፡ በግሉ ዘርፍ የጡረታ መዋጮ፣ በኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታና በመሳሰሉት የግዳጅ ቁጠባ መለመዱ (Forced-saving) ቁጠባን ለማሳደግ ረድቷል፡፡ በአጠቃላይ ከሚሰበሰበው ቁጠባ ውስጥ በባንኮች 80 በመቶ ያህሉ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ በባንኮች ከሚሰበሰበው ቁጠባ ውስጥ ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰበስብ በመሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ከንግድ ባንክ የተረፈውን ለመቀራመት እና ጤናማ ወዳልሆነ ውድድር መግባታቸው ተመላክቷል፡፡ በሌላ በኩል በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ያለው የቁጠባ የወለድ ምጣኔ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከዜሮ በታች (negative-real interest rate) መሆኑ አስቀማጮችን ተጠቃሚ እያደረገ አለመሆኑ የጠቀሱት ተናጋሪዎች በተቃራኒ ተቋማቱ ለሚያበድሩት ገንዘብ የወለድ ምጣኔያቸው ከፍተኛ መሆኑ በደንበኞቹ እና አጠቃላይ በሀገሪቱ ቁልፍ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በቁጠባ መልክ የተሰባሰበው የገንዘብ መጠን ከአገር ውስጥ ምርት አንጻር 24 በመቶን ወደ ኢንቨሰትመንት ከገባው የገንዘብ መጠን 39 በመቶ ጋር ሲነፃፀር የሰፋ ልዩነት (huge deficit) መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል የታየውን ልዩነትም ለመሸፈን መንግሥት በውጭ ፋይናንስ በተለይም በውጭ ብድር ላይ ጥገኛ ሊሆን ችሏል፡፡ በሌላ በኩል የብድር ፍላጎቱ (ጠቅላላ ኢንቨስትመንት) ከሃገር ውስጥ ቁጠባ የበለጠ ሆኖ መገኘቱ በባንኮች መካከል የውድድር መንፈስ እንዳይኖር በማድረግ ባንኮች ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ በተበዳሪዎች ላይ እንዲጭኑ አንዱ ምክንት ሆኗል፡፡

በፋናንስ ዘርፉ የተሠማሩ የቁጠባ ገንዘብ በማሰባሰብ እና አገልግሎታቸውን ተደራሽ በማድረግ ለኢኮኖሚ ልማት አስተዋጽዎ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ከመንግስት ባንኮች ውጪ የግል ባንኮች ለንግድ የሥራ መስክ የአጫጭር ግዜ ብድር ከመስጠት ውጪ ኢኮኖሚውን ለሚያነቃቁ ኢንቨስትመንቶች ፋይናስ ማቅረብ ሰለአለመቻላቸው ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም የግል ባንኮች ሥጋትን በመሸሽ የፕሮጀክት ብድር ለመካከለኛና ለረዥም ግዜ ብድር እየሰጡ ያለመሆናቸው እንደዚሁም ብድር አቅርቦታቸውም በንብረት ዋስትና ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ የፕሮጀክት ሃሳብ ያላቸው ዜጎች የፋይናስ አገልግሎት ለማግኘት እንዳልቻሉ ተብራርቶአል፡፡ ይህ አሠራር የቋሚ ንብረት ዋጋ በየግዜው እየጨመረ እንዲሄድ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ተደረጎ ተወሰዷል፡፡ በተጨማሪም በንብረት ዋስትና ላይ የተመሠረተው የብድር አሰጣጥ ሌሎች አገሮች ላይ እንደተከሰተው የንብረት ዋጋ መዋዠቅ  ቢያጋጥም  አገሪቱን  አደጋ  ላይ  ሊጥል  የሚችል  የፋይናስ  ቀውስ  ሊገጥማት እንደሚችል ተጠቁሞአል፡፡

የፋይናንስ ሴክተሩ የብድር አመላለስ በተመለከተ በእኛ ሀገር ትልቁ ፈተና የመንግስት አካላት ጣልቃ ገብነት መኖሩ መሆኑን የገለጹት ተናጋሪዎች በኢትዮጵያ ችግሩን ከባድ የሚያደረገው በብድር አቅርቦትና አመላለስ ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት መኖሩ መሆኑን በአጽንኦት ተመልክቷል፡፡ ይህም የፋይናንስ ሴክተሩ ለሀገራዊ ልማትና እድገት በሚኖረው ተሳትፎ ላይ እጅግ  አደገኛ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የፕሮጀክቶች ብድር አቅርቦት በአትራፊነቱ ብቻ  ሳይሆን በሚኖራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚገባ በፕሮጀክት ትንተና (analysis) ተደግፎ ቢከናወን ክፋት የለውም ያሉት ተናጋሪዎቹ በብድሩ አመላለስና አጠቃቀም ላይ ቀጣይነትና አግባብነት ያለው የክትትልና ድጋፍ ስርዓት (Monitoring and Follow-up System) መዘርጋት ግዴታ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ከፍተኛ ምጣኔ 5 በመቶ በላይ ከፍ ብሎ እስከ 40 በመቶ መድረሱ ለፋይናንስ ዘርፉ ውድቀት ዓቢይ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

 

4.  የብሔራዊ ባንክ ሚና

የአገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት በበላይነት እንዲመራ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት መጎልበት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ባንኩ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍና የማስፈጸም አቅሙ ደካማ መሆኑ እንደዚሁም በፖለቲካ ተጽእኖ ሥር መውደቁ ለአገራችን የፋይናንስ ስርዓት መዳከም ዓቢይ መንስዔ መሆኑ ተጠቅሶአል፡፡ የብሔራዊ ባንክ የሚመራበት የቁጥጥር ሥርአት በራሱም ሆነ በሚቆጣጠራቸው የፋይናስ ተቋማት ላይ ተጨማሪ ወጪን የሚያስከትል እንጂ የተቋማቱን አቅም መጎልበትና መደገፍ ላይ የተመረኮዘ ባለመሆኑ ውጤታማ አለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

የሀገራችን የፋይናንስ ተቋማት ተወዳዳሪ እና ሀገራዊ ልማት እንዲጎለበት ያላቸው ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ ከላይ የተገለፁት ክፍተቶችን ለመቅረፍ የብሔራዊ ባንክ የሕግ ማዕቀፍ ሊፈተሸ እንደሚገባው፤ በሰው ኃይል እና በዘመናዊ አሠራርና አመራር መለወጥ እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡ በተለይ የፋይናንስ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ለሞባይል ባንኪንግና ለኢተርኔት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ለዚህም ባንኩ ራሱን ማዘመንና በሰው ኃይል ማጠናከር ይጠይቀዋል ተብሎአል፡፡ በተጨማሪም መንግስት ባረቀቀው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በፋይናስ ዘርፉ ላይ ትኩረት በመስጠት የብሔራዊ ባንክን የሕግ ማእቀፍ፣ አሠራር እና ነጻ አደረጃጀት እንዲፈትሽ የሚል ሃሳብ ቀረቦአል፡፡

በመጨረሻ በቀጣይ ተመሳሳይ የፓናል ውይይት በግብርናው ዘርፍ ላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ምሁራን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ተገልጾ የሁለተኛው መድረክ ውይይት ተጠናቋል፡፡